...

በኮቪድ 19 ዙሪያ ችግር ፈቺ ፈጠራዎቸን ያቀረቡ ባለሙያዎች እውቅና እና ሽልማት ተበረከተላቸው

በሃገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለመከላከል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ጋር በጋራ በመሆን covid-19 solution challenge በሚል የተዘጋጀው የፈጠራ ባለሙያዎች የውድድር ፕሮግራም በዛሬው ዕለት የእውቅና እና የሽልማት ስነ ስርዓት ተካሂዷል፡፡ ለአንድ ወር በዘለቀው በዚህ የፈጠራ ባለሙያዎች ውድድር በጠቅላላው 446 ፕሮጀክቶች ቀርበው ከፍተኛ የቴክኒክ ግምገማውን ያለፉ 30 ፕሮጀክቶች ወደቀጣዩ የግምገማ ሂደት ያለፉ መሆናቸውን ያስረዱት የግብረ ሃይሉ ዋና መሪ አቶ ሙሉቀን ቀሬ፤ እጅግ በጥንቃቄ በተለዩ መስፈርቶች አማካኝነትም በፍጥነት ወደስራ ሊገቡ የሚችሉት እና አዋጭነታቸው የተረጋገጡ 12 ፕሮጀክቶች መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህ የፈጠራ ውድድር ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን ያቀረቡ ባለሙያዎች እንደሃገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ያስረዱት የUNDP ተወካይ አቶ ግዛቸው ሲሳይ መሰል እንቅስቃሴዎችን ለማገዝም ተቋሙ የበኩሉን ድርሽ እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡ በዚህ ስነስርዓት አዋጭነታቸው ተረጋግጦ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ ከተመረጡ 12 ፕሮጀክቶች ውስጥ አራት የሚሆኑት የቬንትሌተር መሳሪያዎች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ከእጅ ንክኪ የፀዱ የእጅ መታጠቢያዎች እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ የሶፍትዌር ስራዎች ናቸው፡፡

በዚህ ስነስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተጋበዙት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ክቡር ዶ/ር አብርሃም በላይ በመዝጊያ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከል የቀረቡት የፈጠራ ሃሳቦች በሃገርበቀል ደረጃ እምቅ የፈጠራ ሃብት እንዳለ የተረዳንበት ነው ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስቴሩ አክለውም የተመረጡትን እነዚህን ፕሮጀክቶች ወደመሬት በማውረድ ህበረተሰቡ እንዲጠቀምባቸው ለማድረግ የተሟላ ድጋፍ እንደሚደረግ እና ሌሎች በግሉ ዘርፍ ያሉ ተቋማትም ፈጠራዎቹ ወደ ኮመርሺያላዜሽን እንዲያመሩ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

 

 

 Post Comments(0)

Leave a reply