...

የፈጠራ ባለሙያዎች ስራዎቻቸው ፍሬ የሚያፈራበት ፕላትፎርም ለመፍጠር እንደሚሰራ ተገለፀ

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በዛሬው ዕለት ያዘጋጀውና ዋና ትኩረቱን ሃገራዊ በሆኑ የፈጠራ ፕሮጀክቶች ላይ ያደረገው የአንድ ቀን ወርክሾፕ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት የተወጣጡ ተመራማሪዎች፣ ቴክኖሎጂስቶች እና የፈጠራ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን በኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን እና ሊወሰዱ የሚገቡ የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል፡፡

በወርክሾፑ ጅማሬ ላይ የመክፈቻ ንግግራቸውን ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ ሳ/ማርያም የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ ለአንድ ሃገር ሁለንተናዊ ልማት የሚጫወተውን ከፍተኛ ሚና ጠቅሰው በሃገር ደረጃ የፈጠራ ፕሮጀክቶችን አድቮኬት የሚያደርጉ መሰል ወርክሾፖች መዘጋጀታቸው እጅግ አስፈላጊ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ ምክትል ዋና ደይሬክተሩ በተለይም እንደገለፁት ለየትኛውም ሃገር እድገት ከተፈጥሮ ሃብት ክምችት ባሻገር በዛ ሃብት ላይ የሚሰሩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች እጅግ መሰረታዊ ከመሆናቸው አኳያ አንዲህ ተበታትነው የሚገኙትን የፈጠራ ባለሙያዎች በጋራ በማሰባሰብና ወጥ የሆነ ፕላትፎርም በማዘጋጀት በትብብር የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠር ወሳኝ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

 

በዚህ ወርክሾፕ ላይ የፈጠራ ባለሙያዎችን ወክለው ሰፊ ንግግር ያደረጉት አቶ ወሰንሰገድ መሸሻ በበኩላቸው አትዮጵያውያን በሚታዩ ችግሮች ላይ የተለያዩ ፈጠራዎችን ሰርተው ማቅረብ ቢችሉም የብዙዎች እይታ ወደ ውጭ ያተኮረ በመሆኑ ብቻ የሚሰሩ ስራዎች ፍሬ ሳያፈሩ አንደቀሩ አንስተዋል፡፡ አቶ ወሰንሰገድ በተለይም በጋር በመሆን የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት እና ሃገራዊ ፋይዳቸው እጅግ ከፍተኛ የሆኑ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ፕሮጀክቶችን ለማቅረብ ከተናጥል ይልቅ የህብረት ስራዎች እጅግ ወሳኝ ከመሆናቸው አኳያ ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው ይህ መድረክ ትልቅ ጥቅም እንደሚኖረው ገል ፀዋል፡፡ ከአቶ ወሰንሰገድ በማስቀጠል ስለወርክሾፑ አጠቃላይ ይዘትና አስፈላጊነት ገለፃ ያደረጉት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ አቶ አባይሰው አየለ የስታርታፕ ስራዎችን አሳድጎ ወደ ንግድ ለማሰገባት በሚደረገው ጥረት የፈጠራ ባለሙያዎች እና እንደቴኪኢን ያሉ የመንግስት ተቋማት ማድረግ የሚገባቸውን ጉዳዮች ለመለየት እና ምን ከማን ይጠበቃል የሚለውን ለመመለስ የወርክሾፑ መዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ አንደሚሆን አንስተዋል፡፡

በወርክሾፑ መርሃ ግብር ላይ ለፈጠራ ስራዎች የፋይናንስ ምንጭ ለማግኘት ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ ገለፃ ያደረጉት አቶ ጌታሁን የስታርታፕ ደረጃዎችን በማብራራት ከሃሳብ አልፎ ወደ ትግበራ የገባ የፈጠራ ስራ የፋይናንስ ምንጭ እንደሚያገኝ እና በሃሳብ ደረጃ የሚገኙ የፈጠራ ስራዎች ስጋ ለብሰው ባለመቅረባቸው ብቻ ውጤት ሳይኖራቸው እንደቀረ ገልፀዋል፡፡ ወርክሾፑ ከዚህ መርሃ ግብር በኋላ ሰፊ ግዜውን በተሳታፊዎች ውይይት ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ያሉ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ጉዳይ ሰፊ ምክክር እና ውይይት ተደርጓል፡፡

 

Post Comments(0)

Leave a reply