...

የዲጂታል ፋይናንስን ለማሳደግ የሁሉም ትብብር ወሳኝ አንደሚሆን ተገለፀ

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው የውይይት መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡ ‘‘Digitizing Finance: Mobile Payment’’ በሚል የተሰናዳው ይህ የአንድ ቀን ወርክሾፕ አንደሃገር በዲጂታል ኢኮኖሚው ላይ ያለንበትን ደረጃ፤ ያሉ ችግሮች እና የሚታዩ መልካም እድሎች በማንሳት እንዴት እንምራው ወይም እናሳድገው በሚለው አጀንዳ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ተካሂዷል፡

በወርክሾፑ የተለያዩ የባንክ ተቋማት፣ የዩኒቨርስቲ ሙሁራን እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተሰማሩ ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆን፤ በባለሙያዎች በቀረቡ ሰፊ ትንተናዎች እና የፓናል ውይይቶች ሰፊ ጊዜ በመስጠት ተካሂዷል፡፡ በመርሃግብሩ ጅማሬ ወርክሾፑን በንግግር የከፈቱት የኢኒስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳንዶካን ደበበ የመድረኩ መዘጋጀት በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎችና ሌሎች የንግድ ተቋማት የሚፈጥረውን ወርቃማ እድል አንስተው የዲጂታል ዘርፉን ይበልጥ ለማሳደግ የሁሉም ትብብር እጅግ መሰረታዊ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ የኬኒያን የዲጂታል ፋይናንስ እንቅስቀሴ እንደተሞክሮ በመጥቀስ ኢትዮጵያም ከዚህ ትልቅ ትምህርት መውሰድ እንደሚገባት እና ኢኒስቲትዩቱም እንዲህ ያሉ የውውይት መድረኮችን በማዘጋጀት የፕሮጀክት ሃሳቦች የሚያድጉበትንና የግንዛቤ ስራዎች የሚስፋፉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ወርክሾፕ ሰፊ ትንተና ካቀረቡ ባለሙያዎች መካከል ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ወ/ሪት አንቶኒያ ኢሰር አንዷ ሲሆኑ የዲጂታል ፋይናንስና ቴክኖሎጂ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተራመዱ ያለበትን ሁኔታ እና ሃገራት በዚህ ዘርፍ ውጤት ለማምጣት እየሄዱበት ያለውን ርቀት በጥልቅት አስረድተዋል፡፡ ከሳቸው በማስቀጠል መድረኩን የተረከቡት የቴኪኢን የቀድሞ የስራ ባልደረባ አቶ ዮዳሂ ዘሚካኤል ነባሩ የፋይናንስ ስርዓት በፖሊሲና በመዋቅር ደረጃ በዲጂታል ዘርፉ ላይ የሚኖረውን ጫና በማስረዳት፤ መንግስት እየሄደባቸው ያሉትን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አብራርተዋል፡፡ አቶ ዮዳሂ በተለይም በመሰራት ላይ የሚገኘውን የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ በምሳሌ በማንሳት ሀገሪቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ሃብት ለመፍጠር የሚያስችል ጥሩ መሰራት እንደሚኖራት ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በማስቀጠል መድረኩን የያዙት የቤልካሽ ቴክኖሎጂ ዋና መስራች አቶ ዘውዱ አሰፋ ከድርጅታቸው ተሞክሮ በመነሳት በዲጂታል ፋይናንስ እና የሞባይል ክፍያ ዙሪያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶችንና መልካም እድሎችን አብራርተዋል፡፡ የውርክሾፑ መርሃ ግብር ከእነዚህ አቅርቦቶች በተጨማሪ እጅግ ፍሬያማ በሆኑ የፓናል ወይይቶች የተካሄደ ሲሆን ከተሳታፊ በኩልም ገንቢ አስተያየቶች እና የመፍትሄ ሃሳቦች ተንፀባርቀውበታል፡፡

 

 

Post Comments(0)

Leave a reply