...

ከኮሮና ያገገሙ ሰዎች PTSD በተባለው የአዕምሮ ጤና ቀውስ እንዳይጠቁ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል

በኮሮናቫይረስ ምከንያት በፅኑ ታመው ወደማገገሚያ ክፍል ያመሩ ሰዎች የተለያዩ አሰቃቂ ሁኔታዎች ከተከሰቱ በኋላ በሰዎች ላይ ሊፈጠር ወደሚችል የአዕምሮ ጤና መቃዎስ (post-traumatic stress disorder) እንዳይጋለጡ አስፈላጊው የጤና ክትትል ሊደረግላቸው እንደሚገባ በእንግሊዝ የሚገኝ አንድ የጤና ባለሙያዎች ህብረት አስታውቋል፡፡ በኮሮና ምክንያት ሊከሰት በሚችለው ድህረ የአዕምሮ ጤና ቀውስ ላይ ሰፊ ምርምሮችን ሲያደረግ የቆየው ይህ የጤና ባለሙያዎች ህብረት በፅኑ የህሙማን ክፍል እገዛ ሲደረግላቸው የቆዩ ታካሚዎች PTSD በተባለው የአዕምሮ ጤና ቀውስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን በምርምሩ አስታውቋል፡፡

ይህ የምርምር ውጤት እንዳሳየው ከሆነ በኮሮናቫይረስ ምከንያት በፀኑ ታመው ወደማገገሚያ ክፍል ከሚያመሩ 1000 ሰዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት በዚሁ የአዕምሮ ጤና ቀውስ የመጠቃት እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ እንደተገኘ ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡ ይህ የጤና ቀውስ ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ እንዲል እንደድብርት እና ጭንቀት ያሉ ቀላል የሚመስሉ የጤና ችግሮች ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው በምርምሩ ተገልጿል፡፡

በለንደን በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ለሶስት ሳምንታት በፅኑ የህሙማን ክፍል እገዛ ሲደረግላት የነበረችው ትሬሲ ለምርምር ቡድኑ እንደተናገረቸው ከኮሮናቫይረስ አገግሜ ከሆስፒታሉ መውጣት ብችልም የአዕምሮ ጤናዬ ግን ወደነበረበት ሊመለስ አልቻለም ትላለች፡፡ ትሬሲ እንደምታስረዳው በፅኑ የህሙማን ክፍል በቆየሁባቸው አጭር ሳምንታት ሰዎች ሲሞቱና የማየው ሃኪም ሁሉ በማስክ ተሸፍኖ ስመለከት ፍርሃትና ብቸኘነት በእጅጉ ያስጨንቀኝ ነበር ትላለች፡፡ ይህን የአዕምሮ ጫና በሚቻለው አቅም ለመቋቋም ብዙ ሙከራዎችን አድርጌያለሁ የምትለው ትሬሲ በዚህ ችግር የሚሰቃዩ ብዙ ሺዎች መኖራቸው የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ነው ትላላች፡፡

በኮሮና ምክንያት ሊከሰት በሚችለው ድህረ የአዕምሮ ጤና ቀውስ ላይ ሰፊ ምርምሮችን ሲያደረግ በቆየው የጤና ባለሙያዎች ህብረት ውስጥ ዋና ተሳታፊ የነበሩት ዶ/ር ሚካኤል ብሉምፊልድ እንደሚያብራሩት የዚህ ወረርሽኝ ባህሪ ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው እንዲቆዩ እና እንዲታከሙ የሚያስገድድ የጤና ችግር በመሆኑ እንደ PTSD ያሉ የጤና ቀውሶች የመከሰት እድላቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ያስረዳሉ፡፡ ዶክተሩ ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች በሚቻለው አቅም የአዕምሮ ደህንነታቸው እስኪረጋገጥ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ክትትል እንዲደረግላቸው እና ልዩ ልዩ የጤና ምክሮች በስፋት እንዲያገኙ ማድረግ በረዥም ጊዜ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ መቀነስ ያስችላል ይላሉ፡፡

ምንጭ BBC

 

 

 Post Comments(0)

Leave a reply