...

ጉዳት ያላቸው የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘሮች እየበረከቱ መምጣታቸው ተነገረ

የኮሮናቫይረስ ስረጭትን ለመግታትና ራሳችንንም ከበሽታው ለመከላከል በምናደርገው ጥረት እጅን በሳሙና መታጠብ ወደር የማይገኘለት መከላከያ ነው፡፡ ነግር ግን ውሃ እና ሳሙናን በየሄድንበት ሁሉ ማግኘት ስለማንችል እንደ ሳኒታይዘር ያሉ የእጅ ማፅጃ ዘዴዎች ትልቅ ግልጋሎት ይሰጡናል፡፡ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘሮች በእጆቻችን የምንነካቸውን አያሌ ጀርሞች እና ባክቴሪያዎች በቀላሉ ለማፅዳት የሚያግዙን ቢሆንም ጥቅም ላይ የምናውላቸው አንዳንድ የሳኒታይዘር ውጤቶች ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና ባስ ሲልም ለአደጋ የሚያጋልጡ ሊሆኑ በመቻላቸው የምንመርጣቸውን እነዚህን ሳኒታይዘሮች በጥንቃቄ መመልከቱ ግድ ይላል፡፡

የጤና ተቋማት በተደጋጋሚ እንደሚጠቁሙት ምንግዜም የምንጠቀመው ሳኒታይዘር የያዘው የአልኮል መጠን 60% የማይደርስ ከሆነ በእጆቻችን ላይ የሚገኙ ቫይረሶችን በምንም መልኩ ሊያጠፋ አይችልም፡፡ አንዳንድ ሰዎች የጥራት ደረጃቸው ያልተረጋገጡ ሳኒታይዘሮችን ጥቅም ላይ ከማዋላቸው ባለፈ የአልኮል ይዘታቸው ከፍ ያሉ እንደ ቮድካ እና ካቲካላ ያሉ መጠጦችን እንደ ሳኒታይዘር በመውሰድ ቫይረሱን ለመከላከል የሚሞክሩ አሉ፡፡ ይሁንና ይህ ፈፅሞ የማይመከርና ሰውነታችን ላይም ሌላ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በተደጋጋገሚ ተገልጿል፡፡ እነዚህ መጠጦች ከ30 እስከ 40 የሚገመት የአልኮል መጠን ያላቸው በመሆናቸው ለእጅ ማፅጃ በፍፁም ሊሆኑ አይችሉም፡፡

ሰሞኑን የአሜሪካ የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር ይፋ ባደረገው መረጃ በሃገሪቱ ጥቅም ላይ ከሚውሉና ውደሌሎች የአለም ሃገራት ከሚሰራጩ ሳኒታይዘሮች መካከል ደረጃቸውን ያልጠበቁ እና ጉዳት ሊኖራቸው የሚችሉ ከመቶ በላይ ሳኒታይዘሮች ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ አስተዳደሩ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ ለተጠቃሚዎች እንዳስታወቀው አንዳንድ ሳኒታይዘሮች የሜታኖል ይዘት ያላቸው በመሆናቸው ወደ ቆዳችን ዘልቀው ሲገቡ መርዛማነትና በሂደትም ከባድ ኢንፌከሽኖች ሊፈጥሩ እንደሚችል ይፋ አድርጓል፡፡

አስተዳደሩ ከሰሞኑም እንደጠቆመው በአንዳንድ የሳኒታይዘር ውጤቶች ላይ ወሳኝ የሚባሉ ኢንግሪዲየንቶች ማለትም ethyl ወይም isopropyl የተሰኙ የአልኮል ይዘቶች ከሚገባው በታች ወርደው ስለሚገኙ፤ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘሩ የጥራት ደረጃው ከሚገባው በታች እንዲወርድ እና ሌሎች ጉዳቶችንም ሰዎች ላይ እንዲያደረስ ትልቅ በር እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ ሀገራት መሰል የሳኒታይዘር ውጤቶችን ወደሃገር ውስጥ ሲያስገቡ ፈቃድ ካለው እና ጥራቱ ከተረጋገጠ የመድሀኒት አምራች ሊሆን እንደሚገባ የጠቆመው አስተዳደሩ የሃገረ ውስጥ ምርቶችንም በጥንቃቄ መፈተሸ አንደሚገባ ተናግሯል፡፡

ምንጭ፡ CNN

 

 

 Post Comments(0)

Leave a reply