...

አገራዊ መሰረት የሚጥሉ ግዙፍ የአውቶሜሽን ስርዓቶች በሃገር ልጅ መሰራታቸው ትልቅ አቅም መኖሩን የሚያመላክት ነው

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከፕላንና ልማት ኮሚሽን ጋር በመተባበር ያበለፀገው የዲጂታል ክትትል እና ግምገማ ስርዓት የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስትልጣናት በተገኙበት ተመርቋል ፡፡ በአውቶሜሽን ማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተከበሩ የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮንን አንደሃገር የኢኮኖሚ ሪፎርም ለማምጣት እየተሰራ ያለውን ሰፋፊ ስራ አስታውሰው፤ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ዘማናዊ የአውቶሜሽን ስርዓት የተላበሰ የክትትል እና ግምገማ ስርዓት መጀመሩ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድቷል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ በተለይም እንዳነሱት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እስከሚያልቁ ድረስ ያሉትን ሂደቶች በሚገባ ለመፈተሸ እና ማናቸውንም የእቅድና ሪፖርት ማመላከቻዎችን ጥራት ባለው ሁኔታ መዝግቦ ለማስቀመጥ የአውቶሜሽን መተግበሪያው አስፈላጊነት ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
በስነ ስርዓቱ ላይ ሰፊ ሃሳብ ያነሱት የኢትዮጵያ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ክብርት ዶ/ር ፍፁም አሰፋ እንዳሉት በቴክኖሎጂ የታገዘ የክትትልና ግምገማ ስርዓት የልማት እቅዶች እና ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ፣ ወጪና ጥራት እንዲከናወኑ ከማገዙም በላይ የግልፅኝነትና ተጠያቂነት ስርዓትን ይበልጥ ለማጎልበት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር አብርሃም በላይ በበኩላቸው እንዲህ ያሉ ግዙፍ የአውቶሜሽን ስርዓቶች በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች መሰራታቸው እንደሃገር ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር በማንሳት በስራው ለተሳተፉ ባለሙያዎች በሙሉ ያላቸውን ምስጋና ገልፀዋል፡፡
ይህ የአውቶሜሽን መተግበሪያ በዋናነት የ10 አመቱን መሪ የልማት እቅድን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ እቅዶችና ፕሮጀክቶች የአፈፃፀም ውጤታማነት ለማገዝ እንዲያስችል ታልሞ የተሰራ ሲሆን፤ ከዲዛይን አንስቶ እስከ ፕሮጀክት መጠናቀቂያው ድረስ በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች የተከናነወነ ነው፡፡ በዲጂታል አውቶሜሽን የታገዘው ይህ ዘመናዊ የክትትልና ግምገማ ስርዓት የልማት እቅዶችና ፕሮጀክቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመከታተልና ለመገምገም ትልቁን የመሰረት ድንጋይ የሚጥል ከመሆኑም ባለፈ በተዘጋጀለት የልማት አመላካች ዳሽቦርድ አማካኝነት የሁሉም ተቋማት የስራ አፈፃፀምን ለህዝብ ይፋ ለማድረግ እና ሃገርአቀፍ የእድገት አመላካች ውጤቶችን ዲጂታል በሆነ መልኩ ለውጭው አለም ተደራሽ ለማድረግ ማስቻሉ በእጅጉ የሚለየው ነው፡፡
የዲጂታል ፕላትፎርሙ፤ ከዲዛይን አንስቶ ብልፀጋው በቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ተከናውኗል።


Post Comments(0)

Leave a reply