...

ቀለም እና ብሔራዊ ማንነት

ቀለሞችን አይተን በውስጣችን የሚከሰቱት የደስታ፣ ሀዘን፣ ፍቅር፣ ኩራት እና ሌሎች ስሜቶች በሀገራዊ ማንነታችን ላይ የተመሰረቱ እንደሆነ የሚያሳይ ጥናት በቅርብ ይፋ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህም አጥኚዎች አንድ ሰው ከየትኞቹ ቀለሞች ጋራ የስሜት ትስስር እንዳለው በመመልከት ብቻ ሰውየው የየት ሀገር ሰው እንደሆነ መገመት ችለዋል፤ ከግምቶቻቸው ውስጥም 80 በመቶ ያህሉ ትክክል ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ ከቻይና፣ ጀርመን፣ ግሪክ እና ብሪታንያ የተውጣጡ 711 ሰወዎችን በናሙናነት አካተው ነበር ጥናታቸውን ያከናወኑት፡፡ በጥናቱ ላይ በጎ ፍቃደኝነታቸውን አሳይተው የተገኙት የጥናቱ ተሳታፊዎች እንደ አረንጓዴ፣ ሰማያዊ-አረንጓዴ የመሳሰሉ የቀለማት ስያሜዎችን እንዲያነቡ ተደርገዋል፡፡ በዚህም አማካኝነት ከተቀመጡት 20 የስሜት አይነቶች ውስጥ አዕምሮአቸው ለየትኛው ቀለም ምን አይነት ስሜት እንደሚያሳይ እና ቀለሞቹ ከስሜቶቹ ጋራ ያላቸው የስሜት ትስስር ጥንካሬ ተለክቶበታል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል የብዙዎቹን ስሜት በመቀስቀስ ረገድ ቀይ፣ ጥቁር እና ሮዝ ቀለሞች ቀዳሚዎች ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ቡናማ እና ሀምራዊ አነስተኛ የስሜት መነሳሳትን ሲከስቱ ታይተዋል፡፡ በሌላ መልኩ ጥቁር ቀለም ከሁሉም ሀገራት በመጡት ተሳታፊዎች ዘንድ የሀዘን ስሜትን ገላጭ ሆኖ ሲገኝ ቀይ በበኩሉ እንደ ፍቅር እና ደስታ ያሉ አውንታዊ ስሜቶችን ንዴት እና ጥላቻን ከመሳሰሉት አሉታዊ ስሜቶች አጣምሮ መያዙን በሮያል ሶሳይቲ ኦፕን ሳይንስ ጆርናል ላይ ታትሞ የወጣው ይህ ጥናት አመላክቷል፡፡

ሆኖም እንደየ ዜግነታቸው የተወሰኑ ልዩነቶች ተስተውለዋል፡፡ ለምሳሉ ከጀርመን የመጡት ተሳታፊዎች ከየትኛውም ሀገር በላቀ ቡናማ ቀለም ከአስጸያፊነት ጋራ ሲያስተሳስሩት፤ ከግሪክ የመጡቱ በበኩላቸው ሀምራዊን በዋናነት ከሀዘን ጋራ በማስተሳሰር ብቸኞቹ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በከቻይና የመጡት ተሳታፊዎች ደግሞ ነጭ ቀለም በበለጠ አሉታዊ ስሜትን ሲጭርባቸው (በቻይናዊያን ባህል ቀብር ላይ ነጭ መለበሱን ልብ ይሏል)፤ ቢጫ ቀለም ደግሞ ከግሪኮች በተቀረ በሁሉም ሀገራት ላይ አውንታዊ ስሜትን አጭሯል፡፡

የተሰበሰበን ጥሬ ሀቅ (Data) ወስዶ አንድ ፕሮግራም የሰው ልጆች ወዲያው ሊያስተውሏቸው የማይችሉ ግምት እና ትስስሮችን እንዲያሳይ አድርጎ የሚያሰለጥነውን ማሽን ለርኒንግ የተባለ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) አይነት በመጠቀም ነው ተመራማሪዎቹ የትኛው የጥናቱ ተሳታፊ ከየት ሀገር እንደሆነ ለመለየት የቻሉት፡፡ እንደ ቡድኑ ከሆነ ጥናቱ መሰል ቴክኖሎጂ ለወትሮው ጥሬ ሀቆች ውስብስብ፣ ብዙም ግልፅ ያልሆኑና ለመለየት የሚዳግቱ የሚሆኑበትን የስሜት ጥናት (Emotion Research) ዘርፍን ለመረዳት እንደሚያስችል ጥቁምታን የሰጠ ነው፡፡

ምንጭ፡ Science

 

 

 Post Comments(0)

Leave a reply