...

የደም ዓይነትና ኮቪድ 19

የሰዎች የደም ይነት በኮሮናቫይረስ ከመያዝና በጸና ህመም ከመሰቃየት ጋር ግንኙነት እንዳለው NBC news የተባለ የዜና ማሰራጫ ተቋም በዘገባው አስነብቧል፡፡ እንደማብራሪያው ይህ ማለት ከደም አይነቶች መካከል አንዱ ለወረርሽኙ በጣም ተጋላጭ ያደርጋል የሚል መደምደሚያ ባይኖረውም የሚወጡት ግኝቶች ግን ከመልስ ይልቅ ብዙ ጥያቄዎችን ያስከተሉ ናቸው ተብሏል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የአሜሪካ ሄማቶሎጂ ሶሳይቲ ጆርናል ላይ የወጡት ሁለት ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን በሰዎች የደም ይነት እና በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የሚነሱ ነጥቦችን በሚከተለው መልኩ ቃኝተዋቸዋል፡፡

በመጀመሪያው ጥናት በዴንማርክ 473,654 ሰዎች የኮቪድ ምርመራ ተደርጎላቸው አብዛኞቹ ነጻ ሲሆኑ ቫይረሱ የተገኘባቸው 7,422 ብቻ ነበሩ ይህም ከየካቲት እስከ ሐምሌ ድረስ ያለው መረጃ ነው፡፡ ከደም ዓይነቶች መካከል O በመባል የሚታዎቀው ያላቸው ሰዎች ለSARS-CoV-2 የተጋላጭነት እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡  SARS-CoV-2 ለኮቪድ 19 መነሻ የሆነ ቫይረስ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የጥናቱ ውጤት ከተመረመሩ ሰዎች መካከል 62 በመቶ ያክሉ ብቻ የደም አይነት መረጃ ያላቸው በመሆኑ እጥረት አለበት፡፡ መጠኑ ይነስ እንጂ O የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች የተጋላጭነት እድላቸው የቀነሰ ነው፡፡ 

ሌላኛው ጥናት በካናዳ የተደረገ ሲሆን ለሆስፒታል የሚያበቃ ህመም በገጠማቸው 95 የኮቪድ ታማሚዎች ላይ የተሰራ ነው፡፡ በጥናቱም ከታማሚዎች A ወይም AB የደም ዓነት ያላቸው ሰዎች የመተንፈሻ መሳሪያ ሲስፈልጋቸው ተስተውሏል፡፡ እንዲሁም  በከፍተኛ ክትትል ክፍል (ICU) ውስጥ ረጅም ቆይታ አድርገዋል፡፡ ይህም O ወይም B የደም ዓይነት ካላቸው ሰዎች ጋር ሲነጻጸር ነው፡፡ A ወይም AB የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ኩላሊታቸው የበለጠ ደም ማጣራት እንዲችል የዲያለሲስ እገዛም ተደርጎላቸዋል፡፡ በሁለቱም ጥናቶች ግን ይህ የደም አይነት የተጋላጭነት መጠኑ ዜሮ ነው የሚል ግኝት የለም፡፡   

የማህበረሰብ ጤና ባለሙያዎች የትኛውም የደም ዓይነት ቢኖረንም ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ መከላከያ መንገዶችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ስለ ጥናቱ የWisconsin ሜዲካል ኮሌጅ ሀላፊ የሆኑት Dr. Roy Silverstein ለተጨማሪ ጥናቶች መነሻ የሚሆን ጥናት ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ምንጭ NBC NEWS  Post Comments(0)

Leave a reply