...

ስለ ዝሆን ምን ያህል ያውቃሉ?

ብዙዎቻችን ከልጅነት ጊዜያችን አንስቶ ስለ ዱር ስናስብ በምዕናባችን ከሚከሰቱት እንስሳት መካከል ዝሆኖች ቀዳሚ ናቸው፡፡ ዝሆኖች በምድራችን ከሚራመዱ እንስሳት ሁሉ በግዝፈታቸው ወደር የሌላቸው እና አፈጣጠራቸው ለየት ያሉ ናቸው፡፡ በረጀክሙ ኩምቢ፣ ግዙፍ ግን ልፍስፍስ ጆሮዎች፣ ወፋፍራም እግር ዝሆኖችን ከሌሎች እንስሳት የሚለዩ አካላዊ ገፅታዎቻቸው ናቸው፡፡

ብዙዎቹ ባለሙያዎች በሁለት አህጉራት የሚኖሩ ሁለት አይነት የዝሆን ዝርያዎች መኖራቸው ላይ ይስማማሉ፤ የአፍሪካ (Loxodonta africana) እና የእሲያ (Elephas maximus) ዝሆን ዝርያዎች፡፡ በእነዚህ ሁለት ዝርያዎች ስር የተለያዩ ቅርንጫረፍ ዝርያዎች አሉ፤ ምንም እንኳን ምን ያህል ናቸው በሚለው ላይ ክርክር ቢኖርም፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች የሳር ምድር (Loxodonta africana) እና የጫካ (Loxodonta cyclotis) ተብለው የተከፈሉ ሁለት የዘር ቅርንጫፍ ሲኖራቸው የእሲያዎቹ በበኩላቸው የህንድ (Elephas maximus indicus)፣ ስሪ ላንካ (Elephas maximus maximus) እና ሱማትራ (Elephas maximus sumatranus) የተሰኙ የዘር ቅርንጫፎች አሏቸው፡፡

የአፍሪካና እሲያ ዝሆኖች ልዩነት

የአፍሪካ ዝሆኖች ከሰሃራ በታች ባለው የአህጉራችን ክፍል በተለያዩ ስፍራዎች ይኖራሉ፡፡ የእሲያ ዝሆኖች በበኩላቸው በኔፓል፣ ህንድ እና ደቡብ ምስራቅ እሲያ ጫካዎች ኑሯቸውን አድርገዋል፡፡ በግዝፈት ያነፃፀርን እንደሆነ የአፍሪካ ዝሆኖች ብልጫውን ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡  ቁመታቸው ከ2.5 እስከ 4 ሜትር ሊደርስ ሲችል ክብደታቸውም ከ2,200 ኪ.ግ እስከ 6,350 ኪ.ግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የእሲያ  ዝሆኖች ከ2 እስከ 3 ሜትር ብቻ ሲረዝም ክብደታቸውም ከ2,000 እስከ 5,000 ኪ.ግ ብቻ ነው፡፡

ሁለቱ የዝሆን ዝርያዎች ከግዝፈትም ባሻገር ሌሎች ጥቂት ልዩነቶች አሏቸው፡፡ የአፍሪካ ዝሆኖች ጆሮ ገዘፍ ያለና ቅርፁም የአፍሪካ ካርታን የመሰለ ሲሆን የእሲያዎቹ ዝሆኖች በበኩሉ አነስ ያለና ክብ ቅርፅን የያዘ ነው፡፡ ወንዶቹም ሆነ ሴት የአፍሪካ ዝሆኖች ትላልቅ ጥርስና እቃ ለማንሳት የሚረዳ ሁለት ጣት መሰል ነገር በኩምቢያቸው ጫፍ አላቸው፡፡ የእሲያ ዝሆኖች በኩምቢያቸው ላይ ያለው ጣት አንድ ብቻ ሲሆን ረጃጅም ጥርስ የሚያበቅሉትም ወንዶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ሴቶቹ እና አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የእሲያ ዝሆኖች አነስተኛ መጠኑ አነስ ያለ ጥርስን ሲያበቅሉ ጥርሱ ወደ ውጪ ግን የማይታይ ሊሆን ይችላል፡፡

የዝሆን ጥርስ ግዙፍና ረጅም ስር ያላቸው ሲሆን ለዝሆኖቹ መቆፈርያ፣ እቃ ማንሻ፣ ምግብ መሰብሰብያ እና እራሳቸውን መከላከያ ሆኖ ሲያገለግላቸው ኩምቢውንም የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ እኛ የሰው ልጆች ግራኝ ወይም የቀኝ እጅ ተጠቃሚ እንደሆንነው ሁሉ ዝሆኖችም ግራኝ አልያም የቀኝ ቀንዳቸውን ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የትኛውን እንደሚጠቀሙ ለማወቅ ቀላሉ መንገድ የደከመውን መለየት ነው፡፡

ሁለቱም የዝሆን ዝርያዎች የተለያዩ የሳር አይነቶችን፣ ፍራፍሬዎችን፣ ቅጠላ ቅጠሎችን፣ የዛፍ ቅርፊት እና ስር የመሳሰሉ የእፅዋት አካላትን ይመገባሉ፡፡ በቀን ውስጥ 16 ሰዓታትንም በመመገብ የሚያጠፉና በዚህም ከ75 እስከ 150 ኪ.ግ የሚሆን ምግብ የሚሰለቅጡ ናቸው፡፡

ማህበራዊ ህይወት

የዝሆኖች ቡድን ዕድሜያቸው በገፋ ሴቶች የሚመራ ነው፡፡ መንጋው በዋናነት በሴት ቤተሰቦችና ህፃናት ዝሆኖች ሲሞላ እንደ ምግብ አቅርቦቱ ከ6 እስከ 20 አባላትን ሊይዝ ይችላል፡፡ ቤተሰቡ ከሚፈለገው በላይ ሲበዛ በቅርብ አካባቢ ወደሚሰፍሩ የተለያዩ ቡድኖች ይከፈላል፡፡ መሪዋ ዝሆን ተግባሯን የምታከናውነው ልምዷን እና የትኛው ስፍራ ጥሩ ምግብ እና መጠለያ እንደያዘ የሚነግራት ትውስታዋን በመጠቀም ነው፡፡ በተጨማሪም ህፃናት ዝሆኖችን ከሌሎቹ ጋራ እንዴት መግባባት አንዳለባቸው የማስተማሩን ድርሻ ይወጣሉ፡፡

ዝሆኖች በከፍተኛ ሁኔታ ማህራዊ ኑሮን ከሚመሩ እንስሳት መካከል ናቸው፡፡ አንድ ዝሆን ከሌላው ጋራ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን የሰው ልጆች መስማት የማንችለውን አነስተኛ ድምፅ በማውጣትም ከሶስት ኪ.ሜ በላይ ርቆ ያለ ዝሆንን መለየት ይችላሉ፡፡ በራሳቸውም ሆነ ሌላ ቡድን ውስጥ ላለ ዝሆንም መልካም ስነ-ምግባር በማሳየትም ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ ሲገናኙ ኩምቢያቸውን ወደላይ ከፍ በማድረግ አልያም የኩምቢያቸውን ጫፍ ወደ ሌላኛው ዝሆን አፍ በመክተት ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በመንጋቸው ውስጥ ያለ ሌላ የተጎዳ አባል ካለ የሚጠብቁና ስለሌላው የቡድኑ አባል ደህንነት ግድ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡

በሌላ መልኩ ዝሆኖች በማሰብ ችሎታቸው የማይታሙ መናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሆነው ውስብስብ ችግሮችን የመፍታት ብቃት ሲያሳዩ እንዲሁም ለቅሶ ሲደርሱና ሲያፅናኑ መታየታቸው ነው፡፡

ዕድሜ

ዝሆኖች ከተወለዱ ከ8 እስከ 13 ባሉት ዓመታት ውስጥ ለፆታዊ ግንኙነት ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ሰዓት ምግባቸውን ፈልገው ማግኘት እና እራሳቸውን መጠበቅ እስከቻሉ ድረስ ወንድ ዝሆኖች መንጋውን ትተው በመውጣት ለብቻቸው አልያም ከሌሎች መሰሎቻቸው ጋራ በአነስተኛ ቡድን ኑሮዋቸውን ይመራሉ፡፡

ሴቶቹ ዝሆኖች በአስራዎቹ አጋማሽ ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ልጅ የማይወልዱ ሲሆን ወንዶቹ ግን ዕድሜያቸው ሰላሳዎቹ ውስጥ እስከሚገባ ድረስም ልጅ ላይወልዱ ይችላሉ፡፡ አንድ የዝሆን ልጅ የሚወለደው ከ22 ወራት የእርግዝና ቆይታ በኋላ ነው፡፡ የሚወለዱት ጨቅላ ዝሆኖችም ከ68 እስከ 158 ኪ.ግ ክብደትና 90 ሴ.ሜ አካባቢ ቁመት ይዘው ይህችን ምድር ይቀላቀላሉ፡፡ በተጨማሪም ፀጉር እንዲሁም ረጅም ጭራና አጭር ኩምቢ ያላቸው ናቸው፡፡ ዕድገታቸው ግን እጅግ ፈጣን የሚባል ነው፤ በተወለዱ በአንድ ዓመት ውስጥ በየቀኑ ከ0.9 እስከ 1.3 ኪ.ግ እየጨመሩ ይሄዳሉ፡፡ ሶስት ዓመት ሲሞላቸውም መደበኛ ምግብ መመገብ ይጀምራሉ፡፡

አለም አቀፉ የተፈጥሮ እና የተፈጥሮ ሀብቶች ሕብረት (IUCN) የእሲያ ዝሆኖች የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ሲል ያስቀምጣቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ሙሉ ቁጥራቸው ባይታወቅም እየቀነሱ መሆናቸው ግን ይታመናል፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካ ዝሆኖች ቁጥራቸው በመጨመር ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓትም 415,000 የአፍሪካ ዝሆኖች በየዱሩ ይገኛሉ፡፡ በአደጋ ስጋት ረገድ የአፍሪካንም ሆነ የእሲያ የዝሆን ዝርያዎችን የሚያመሳስላቸው የአደን እና የዘር ቅርንጫፎች የመጥፋት ስጋት የተጋረጠባቸው መሆኑ ነው፡፡

ምንጭ፡ Live Science

 

 Post Comments(2)

...
dobsonz3 days, 5 hours ago

ltTzuO http://pills2sale.com/ levitra nizagara

...
dobsonz3 days, 10 hours ago

T1kMaW http://pills2sale.com/ levitra nizagara

Leave a reply