...

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቴሌኮምዩኒኬሽን ልማት ጉባኤ ልታስተናግድ ነው

በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የዓለም የቴሌኮምዩኒኬሽን ልማት ጉባኤ (WTDC) 2021ድን ለማስተናገድ የሚያስችላትን ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በሚደረገው በዚህ ጉባኤ ላይ ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ 2500 ታላላቅ የዘርፉ ተዋንያን የሚሳተፉበት ሲሆን በየ አራት ዓመት አንዴም የሚከናወን ነው፡፡ ከዓለም ዙርያ የተውጣጡ 240 ያህል ግለሰቦች ተሳታፊ በሆኑበት በዚህ የፊርማና ውይይት ስነ-ስርዓት  ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር አህመዲን መሐመድ የስምምነት ፊርማቸውን ሲያኖሩ በተባበሩት መንግስታት የዓለም አቀፍ ቴሌኮምዩኒኬሽን ህብረትን ወክለው ደግሞ ዋና ፀሀፊው አቶ ሆውሊን ዣው ፈርመዋል፡፡

እንደዚህ አይነቱን ጉባኤ ለማዘጋጀት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሀገር መሆኗ ለኢትዮጵያ ክብር እንደሆነ  ያወሱት ዶ/ር አህመዲን ጉባኤውን የማዘጋጀቱ ውሳኔም ኢትዮጵያም ሆነ አፍሪካ ዲጂታል ልማትን ለዘላቂ ልማታቸው መስፈንጠርያ አድርገው በቀዳሚነት ለመውሰዳቸው ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አህመዲን ሀገራች ለምታከናውነው የዲጂታል ምጣኔ-ሐብት ግንባታ ቁልፍ ተዋፅዖ እንደሚኖረው የሚጠበቀውን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂንም ለተሳታፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

አቶ ሆውሊን ዦው በበኩላቸው በአህጉሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከናወነው በዚህ ጉባኤ ላይ ወሳኝ የተለያዩ ጉዳዮች እንደሚዳሰሱበት በመጥቀስ ወጣቶች የኮንፈረን ዋና ትኩረት መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

ስድስት ዋና ዋና አብይ ጉዳዮችን (ትብብር፣ ተካታችነትን፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ አመራር፣ ኢኖቬሽን እና ወጣቶች) ማዕከል አድርጎ የሚዘጋጀው የ2021 የዓለም የቴሌኮምኒኬሽን ልማት ጉባኤ በዘርፉ ዙርያ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን የሚያቀርብ እና በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋራ ተዋደው መሄዳቸውንም የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ጉባኤው በቀጣዩ ዓመት 2014 ላይ ከጥቅምት 30 እስከ ህዳር 10 ድረስ ባሉት 11 ቀናት ውስጥ የሚደረግ ሲሆን ከዚያ በማስቀደም ግን መዳረሻ የሚሆኑ ሌሎች ተያያዥ ጉባኤዎች በዓመቱ ውስጥ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ እንዲዘጋጅ ትልቅ ጥረት መደረጉን የገለፁት ዶ/ር አህመዲን ሀገራችን የቀረፀችው ሀገር በቀል የልማት እቅድ እና እተከናወኑ ያሉት የተለያዩ ዘርፎችን የሚሸፍኑ የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ ተመራጭ ሆና ጉባኤውን እንድታስተናግድ እንዳስቻሏት አስረድተዋል፡፡ ለኮንፈረንሱ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለ ድርሻ ተቋማትን ያካተተና የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚመራው ሀገር አቀፍ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም 10 ንዑስ ኮሚቴዎችን አዋቅሮ እንቅስቃሴውን እንደጀመረ ሚኒስትር ደኤታው ገልፀዋል፡፡

ኮንፈረንሱ በኢትዮጵያ ከመዘጋጀቱም ባሻገር አፍሪካን የሚመስል እንደሚሆን በመግለፅ እንደ አለባበስ እና አመጋገብ ያሉት የተለያዩ አፍሪካ ባህል መገለጫዎች እንዲወከሉበት እንደሚሰራና እስካሁንም ይህን የሚያሳኩ ስራዎችን ከአፍሪካ ሀገራት ጋራ በመሆን መሰራት መጀመሩን አክለው ተናግረዋል፡፡Post Comments(0)

Leave a reply