...

የኮቪድ-19ኝን መነሻ መመርመር እንደሚጀምር የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ መነሻን ለመመርመር ማቀዱን ይፋ አድርጓል፡፡ ጥናቱ በቅድሚያ ቫይረሱ የታየባትን የቻናዋን ዉሀን ከተማ ሚመረምር ሲሆን በማስከተልም ወደ መላው ቻይና እና ሌሎች ሀገራት አድማሱን ያሰፋል፡፡ ታድያ ይሳካል ብለን ብናስብ እንኳን የቫይረሱን መነሻ ማወቅ ዓመታትን ሊወስድ እና ብዙ ፖለቲካዊ ትኩሳቶችንም ሊነካካ ይችላል፡፡

ምርመራውን እስካሁን ይፋ ያልተደረጉ ዓለም አቀፍ የበሽታ ስርጭት አጥኚዎችን (epidemiologists)፣ የስነ ቫይረስ አጥኚዎችን (virologists) እንዲሁም በህብረተሰብ ጤና፣ እንስሳት ጤና እና ምግብ ደህንነት ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው አጥኚዎች የሚመሩት ይሆናል፡፡ እንደ ድርጅቱ ከሆነ በዉሀን የሚደረገው የመጀመሪያው ምርመራ እዚያው ባሉ ቻይናውያን አጥኚዎች አማካኝነት የሚደረግ ሲሆን ዓለም አቀፍ የአጥኚዎች ቡድን ወደ ስፍራው የሚያቀናውም በዚህ የመጀመሪያ ጥናት የሚቀርቡትን ውጤቶች ከተመለከተ በኋላ ነው፡፡

በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠባቸው የሚጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ ጎብኝተውት የነበረውና በቫይሱ ስርጭት ላይ የተጫወተው ሚና እስካሁንም በዝርዝር የማይታወቀውን ሁአናን የባህር ምግቦች ገበያ በጥናቱ በስፋት ይዳሰሳል፡፡ ከዚህ ቀደም ገበያው ላይ ከነበሩ ማቀዝቀዣዎች የተወሰዱ የስጋ ናሙናዎች ላይ በአንዳቸውም ቫይረሱ (SARS-CoV-2) አልተገኘም ነበረ፡፡ ሆኖም ከአካባቢው በተወሰዱ የቆሻሻ ውሃ ፍሳሾች ላይ በተደረገ ምርመራ ግን ቫይረሱ ተገኝቷል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት ልዑኩ በገበያው ላይ ሲሸጡ የነበሩ በግብርና የተራቡ እንዲሁም እንደ ቀበሮ፣ ራኩን፣ የሲካ አጋዘን የመሳሰሉ የዱር እንስሳትን የሚመረምር ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ቡድኑ ሌሎች በዉሀን የሚገኙ ገበያዎችን የሚመረምር እና እንስሳቱ በቻይና እንዲሁም ከድንበር ባሻገር ያደረጉትን ጉዞ የሚቃኝ ይሆናል፡፡ በዋናነት ግን በቫይረሱ በመጠቃት የሚታወቁት እንደ ድመት እና ሚንክ ያሉ እንስሳት ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ሆናል፡፡

የምርመራ ቡድኑ በተጨማሪነትም ከታህሳስ በፊት የቫይረሱ ስርጭት ከነበረም የሚመለከት ይሆናል፡፡ በቀዳሚነት ወረርሺኙ የተገኘባቸውን ሰዎችን በማነጋገር የት ተይዘው ሊሆን እንደሚችል የማጣራት እና ከታህሳስ በፊት ባሉት ሳምንታት ብሎም ወራት ውስጥ በጤናና ሌሎች ባለሙያዎች የተሰበሰቡ የደም ናሙናዎችን እንዲሁም የተሰጡ ፀረ ባህቴሪያ መድሃኒቶችን የመመርመር ስራዎችን ማከናወንም ከቡድኑ  ይጠበቅበታል፡፡

የዚህ ምርመራ ዕቅድ ይፋ መሆንን ተከትሎ ከወዲሁ ምርመራው የተለያዩ ጉዳዮችን አድማሱን በማስፋት ብዙ ያልተባለባቸው ነገሮችንንም  የሚመለከት እንዲሆን ባለሙያዎች በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡ ከቻይና ውጭ ባሉ የሌሊት ወፎች ላይም የቫይረሱ ቅርብ ዘመዶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ሀሳብ በተለያዩ ባለሙያዎች ተቀባይነትን እያገኘ መጥቷል፡፡ በዚህም መነሻነት ይመስል የምርምር ቡድኑ ትኩረቱ ከቻይናም ባሻገር ማስፋት እንዳለበት የሚመክሩ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ለፀጉራቸው ተበለው እንዲራቡ የሚደረጉትን እንደ ራኩን፣ ውሻ እና ዝባድ ያሉ አጥቢ እንስሳትንም መመልከት እንደሚገባ ተነግሯል፡፡ በዚህ ረገድ ጥናቱ በሳይን የሚመራ እና ለሀሳብ ክፍት ሆኖ ጠቃሚ ሀሳቦችን ሁሉ የሚመለከት እንደሚሆን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡

ብዙ የዘርፉ አጥኚዎች በሽታው ከሌሊት ወፎች መነሳቱን ቢያምኑም እንዴት ወደ ሰው ልጆች ሊተላለፍ ቻለ የሚለው ግን እስካሁንም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው፡፡

ምንጭ፡ Nature

 Post Comments(0)

Leave a reply