...

ፋብላብ አዲስ እና ላይታውስ ስልጠና እና አማካሪ ከኢንስቲትዩቱ ጋር ስምምነት ፈፀሙ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማሳቹሴት ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ፋብላብ ማዕከልና ላይታውስ ስልጠና እና አማካሪ ድርጅት ከቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ጋር ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ፈርመዋል፡፡ ተቋማቶቹ በተለያዩ የፈጠራ ስራ ውጤቶች፣ አቅም ግንባታ፣ ሚዲያን ለማህበረሰባዊ ለውጥ መጠቀም እና ሌሎችም አበይት ጉዳዮች ላይ ነው ከኢንስቲትዩቱ ጋራ ለመስራት የተስማሙት፡፡

ላይታውስ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ቤተሰቦችን በአመራር እና አቅም ግንባታ ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችን ለመስጠትና ከኢንስቲትዩቱ ጋርም የገበያ ድጋፍ፣ የሰው ኃይል አቅርቦት እና የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ በአንድላይ ለመስራት የተስማማ ሲሆን ኢንስቲትዩቱም የመረጃ፣ ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ፋብላብ አዲስም እንዲሁ ከኢንስቲትዩቱ ጋር የፈጠራ ስራዎችንና መሰረተ ልማትን በጋራ ለመጠቀም፣ አገራዊ ጥቅምና የስራ ዕድል ፈጠራ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በማልማት ወደ ኢንተርፕራይዝ ለማሳደግ፣ ኤግዚቢሽኖች ላይ በጋራ ለማስተዋወቅ፣ ጥልቅ ምርምርን ለሚፈልጉ ፕሮጀክቶች የማማከር ስራ ለመስራት እና ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ ችግር ፈቺ የሆኑ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ስምምነት አካሂዷል፡፡

በፊርማ ስነ ስርዓቶቹ ላይ ለሁለቱም ድርጅቶች ተቋማዊ መዋቅር፣ ተግባራት እና ሌሎች ኢንስቲትዩቱን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙርያ በአቶ ዳውድ መሐመድ አማካኝነት ገለፃ ቀርቧል፡፡

ስምምነቶቹ ተቋማቱ ከኢንስቲትዩቱ ጋራ ባላቸው የዓላማ መመሳሰል ሳብያ የመጡ ናቸው ያሉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ ኢንስቲትዩቱ የሚጎሉትን ነገሮች ለመሙላት እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

ተቋማቸውን ወክለው ስምምነቱን የተፈራረሙት የላይታውስ እና ፋብላብ ዋና ኃላፊዎች አቶ እስክንድር በላይ እና አቶ ሀብታሙ አገኘው ከኢንስቲትዩቱ ጋራ ትብብር መፍጠሩ ትልቅ እርምጃ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን በጋራ መስራቱም እንደ ሀገር ስኬታማ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡Post Comments(0)

Leave a reply