...

ጁፒተር መሳይዋ ደመና አልባ ፕላኔት

ተመራማሪዎች በስነ-ፈለክ ምርምር ውስጥ የመጀመሪያ የሆነ ጁፒተርን የሚመስል ደመና አልባ ፕላኔት ማግኘታቸውን አሳወቁ፡፡ ስለ ፕላኔቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍንጭ የተገኘው በ2012 ቢሆንም ከባቢ አየሩ ግን እስካሁን ድረስ ሳይታወቅ ቆይቷል፡፡ ሞቃቱ ጁፒተር የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው በሳይንሳዊ መጠሪያው WASP-62b የሚባል ሲሆን በስርዓተ ፀሐይ ውስጥ ከሚገኘው ጁፒተር ግማሽ ያክል መጠን ሲኖረው በ575 የብርሃን ዓመት ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

ፕላኔቱ ፀሐይን ለመዞር 12 ዓመት ከሚወስድበት ከጁፒተር በተቃራኒው የራሱን ኮከብ ዞሮ ለመጨረስ አራት ቀን ተኩል ብቻ ይፈጅበታል፡፡ ለኮከቡ ባለው ቅርበት የተነሳ ከፍተኛ ሙቀት አለው፡፡ ለዚህም ነው ተመራማሪዎቹ ሞቃቱ ጁፒተር ሲሉ የሰየሙት፡፡

ለምርምሩ ሃብል የተባለው የህዋ ቴሌስኮፕ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን በውስጡ የሚገኙ ንጥረ ነገሮችን ለመለየት ስፔስትሮስኮፒ የተባለ ስልትን እንደተጠቀመች ምርምሩን ያደረገችው ሙንዛ አላም ተናግራለች፡፡ ምንም እንኳን ፖታሺየም መኖርን የሚያመለክት ፍንጭ ባይኖርም ሶዲየም የተባለው ንጥረ ነገር ግን በግልጽ ይታያል ስትል አስረድታለች፡፡

ደመና አልባ ፕላኔቶችን የማግኘት እድል እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነ የምትናገረው አላን እስካሁን ባለው ምርምር ግልጽ የሆነ ከባቢ አየር ያለው ኤግዞ ፕላኔት ሞቃቱ ሳተርን የተሰኘውና በ2018 የተገኘው WASP-96b ፕላኔት መሆኑን ገልጻለች፡፡ የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች እንዲህ አይነት ግልጽ የሆነ ከባቢ አየር ያላቸውን ፕላኔቶች ማጥናት በፕላኔቶች አፈጣጠር ዙሪያ ለሚደረገው ምርምር አጋዥ ይሆናል ብለዋል፡፡

ምንጭ PHYS.ORGPost Comments(0)

Leave a reply