...

ሳኒታይዘሮች የህፃናት ዓይን ላይ አሳሳቢ ጉዳት እያደረሱ ነው

ከአንድ አመት በፊት የኮቪድ-19 ወረርሺኝ መቀስቀሱን ተከትሎ የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘሮችን መጠቀም ዕለታዊ ተግባራችን ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ እነዚህ ሳኒታይዘሮች እጃችንን ሲያደርቁትና ሽታቸውም በዓይናችን እንባ ሲያቀር ቢቆይም ያሳለፍነው ሐሙስ የወጣ ጥናት እንደሚያሳየው ግን እስከ አይነ ስውርነት ሊያደርስ በሚችል ሁኔታ አይናቸው ውስጥ ሳኒታይዘር የሚገኝባቸው ህፃናት ቁጥር እያደገ መጥቷል፡፡

በአውሮፓውያኑ 2019 ሳኒታይዘር ህፃናት ለኬሚካል ካላቸው ተጋላጭነት ውስጥ የ1.3 በመቶውን ድርሻ ብቻ ይወስድ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር በፍጥነት አድጎ በ2020 መጨረሻ ላይ 9.9 በመቶ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ አንድ ትንሽ ህፃን ብቻ በፈረንሳይ ዓይኑ ውስጥ በተገኘ ሳኒታይዘር ሳብያ በሆስፒታል ቆይቶ ህክምና ለመከታተል ተገዶ የነበረ ቢሆንም በ2020 ቁጥሩ ወደ 16 ከፍ ብሏል፡፡ በሌላ ጥናትም ህንድ ውስጥ በሳኒታይዘር ሳብያ ሁለት ትናንሽ ህፃናት ከፍተኛ የዓይን ጤና ችግር ውስጥ ገብተው ነበር፤ የኋላ ኋላ በተደረገላቸው ርብርብ ሙሉ ለሙሉ ቢያገግሙም፡፡

የእጅ ማፅጃ ሳኒታይዘሮች ከፍተኛ የአልኮል መጠን በተለይም በኢታኖል መልኩ ስለሚይዙ ኮርኒያ ተብሎ በሚታወቀው የአይናችን ክፍል ውስጥ ያሉትን አንዳንድ ሕዋሳት ሊገድሉ ይችላሉ፡፡ ትናንሽ ህፃናት ደግሞ ከቁመታቸው ማጠር የተነሳ ሳኒታይዘሩ ሲረጭ ቀጥታ ወደ አይናቸው ተፈናጥሮ የመግባት ዕድሉ ከፍ ስለሚል ለዚህ በተለየ ተጋላጭ ናቸው፡፡ አንዳንድ ህፃናት ደግሞ ይባስ ብሎ ሳኒታይዘሩ እጃቸው ላይ ከተደረገላቸው በኋላ ወዲያው አይናቸውን ይነካካሉ፡፡ ቀዳሚው ስጋት ግን በህዝብ መሰብሰቢያ አካባቢዎች ብዙን ጊዜ ሳኒታይዘር የሚረጨው የህፃናቱ አይን በሚገኝበት ቁመት ገደማ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ በወርሀ ግንቦት ፈረንሳይ ውስጥ ሳኒታይዘር በአይናቸው ከገባባቸው ህፃናት መካከል 16.4 በመቶው ብቻ በነዚህ ስፍራዎች ቢሆንም ነሀሴ ላይ ግን መጠኑ ወደ 52.4 ሊያድግ ችሏል፡፡

ታድያ ይህን ችግር ለመከላከል ከሳኒታይዘር ይልቅ በማፅዳት ረገድም የተሻለ የሆነውን እጅን በውሃና ሳሙና መታጠብ ቀዳሚ ምርጫ ሊሆንና ወላጆችም የእነርሱ መጠንቀቅ እንዳለ ሆኖ ልጆቻቸው እንዴት ሳኒታይዘር በትክክል መርጨት እንዳለባቸው ማስተማር እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ ሆኖም ሳኒታይዘሩ የህፃናት አይን ውስጥ (ወይም አዋቂ ውስጥም ቢሆን) የሚገባ ከሆነ ተከታዮቹን እርምጃዎች በአስቸኳይ መውሰድ ይገባል፡-

፩. አይናቸውን እንዳያሻሹ ማድረግ (ችግሩን በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚያባብሰው)፤

፪. ሳኒታይዘሩ የተረጨበትን አይን ትንሽ ሞቅ ባለ ውሃ ለአስር ደቂቃ ማጠብ፤

፫. ህመሙና ማቃጠሉ ከቀጠለ ወይም የማየት እክል ከገጠማቸው ግን ህፃናቱን በፍጥነት ወደ አይን ሀኪሞች ወይም ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ማስገባት ይገባል፡፡

ምንጭ፡ Live SciencePost Comments(0)

Leave a reply