...

ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ የሃገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት በአምስቱ ሴንተሮች የሚገኙ ተመራማሪዎችንና ፈጻሚዎችን የሚያስተዋውቅና በ2012ዓ.ም ተቋሙ ሲያከናውናቸው በነበሩ ተግባራት ለመጣው ውጤት የተሻለ አፈጻጸም ለነበራቸው የተቋሙ ሰራተኞችና ፈጻሚዎች በትላንትናው ዕለት የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡ በእንጦጦ ፓርክ በተዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር የተቋሙ ቤተሰቦች የተሳተፉበት የጠዋትና የከሰዓት ዝግጅቶች ተካሂደዋል፡፡ የጥዋቱ መርሃ ግብር አራት ኪሎ ከሚገኘው የተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት ወደ አዲሱ የእንጦጦ ፓርክ በተደረገ ጉዞ ተጀምሯል፡፡ በፓርኩ ውስጥ እሴት በተጨመረበትና በተፈጥሮ በተዋበው ጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ የተካሄደ ሲሆን የጥዋቱ መርሃ ግብርም አዝናኝ በነበረው የፈረስ ግልቢያ ውድድር ተጠናቋል፡፡

የከሰዓት በኋላው ዝግጅት ከምሳ ግብዣ በኋላ የቀጠለ ሲሆን የዚህን ዝግጅት መክፈቻ የቷቋሙ ዋና ዳሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ በንግግር አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ንግግራቸውን ላለፉት ጊዜያት እንደ አለም እና እንደ ሀገር በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ማለፋችንን አስታውሰው የጀመሩ ሲሆን በተደራረበ ችግር ውስጥም ቢሆን የቴክኢን ቤተሰቦች ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ ስራዎች መስራታቸውን አስገንዝበዋል፡፡ አቶ ሙሉቀን አክለውም ‹‹ቴክኢን ሰው ነው፤ ሰው ያስባል፣ ያቅዳል እንዲሁም ይፈጽማል፡፡ ስለዚህ በተቋሙ ውስጥ ያሉ ተመራማሪዎችና ሁሉም ሰራተኞች ያላቸውን የማሰብ፣ የመፍጠርና የመፈጸም አቅም በብቃት መጠቀም አስፈላጊ ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለባትን የፈጠራ፣ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር ክፍተት ለመሙላት ታስቦ  በተደራጀ ተቋም ውስጥ የምንሰራ ሙያተኞች የሀገራችንንና የህዝቦቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ችግር ፈቺ ስልጠና፣ ምርምርና ቢዝነስ ተኮር ተግባራትን በመስራት የበኩላችንን ሀላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉ አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

በንግግራቸው ማብቂያ ላይም አቶ ሙሉቀን ፕሮግራሙ የተዘጋጀው አምስቱን የተቋሙን ሴንተሮች ማቀላቀል፣ ባለፉት ጊዜያት የተሰሩ ስራዎች በተቋሙ ሰራተኞች የተከናወኑ በመሆናቸው ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላላቸው ተመራማሪዎችና ፈጻሚዎችን ለማበረታታትና በስድስት ወር ውስጥ በአስደናቂ ጥራትና ፍጥነት ከተሰራው ፓርክ ልምድ መውሰድ የሚሉ ሶስት አላማዎችን ያነገበ እንደሆነ  ተናግረዋል፡፡

በመቀጠልም የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ተሾመ ከጥቂት ዓመታት በፊት ተቋሙ በሰው ሃይልና በመፈጸም አቅም የነበረበትን ሁኔታ አስታውሰው ዛሬ ላይ ከ340 በላይ ሰራተኞችን ሲይዝና በአምስት ሴንተሮች ሲደራጅ ተጨማሪ ሀላፊነቶችንም በመጨመር ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ተቋማችን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና ተቋማት የተሸለ የአሰራር ስርዓት እንዲኖራቸው የሚጠበቅብንን ሀላፊነት መወጣት አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከተቋሙ ሃላፊዎች በተጨማሪም ተጋባዥ እንግዳ የነበረው አዲስ ቡርሃን (ሙሃመድ አሊ ቡርሃን) ለተቋሙ ሰራተኞች በጣም ጠቃሚ የሆነ በማሰብና በአእምሮ ብቃት ላይ ያተኮረ ንግግርን አቅርቧል፡፡ ከቀረበው ንግግርም በመነሳት ታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን አዲስም ምላሾችን ሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም በ2012 በተቋሙ ውስጥ የተሻለ አፈጻጸም የነበራቸው ተመራማሪዎችና ሌሎች ፈጻሚዎች የተዘጋጀላቸውን የምስክር ወረቀት እና የማበረታቻ ሽልማት ከተቋሙ ዋና ዳይሬክተር እጅ ተቀብለዋል፡፡ ዝግጅቱም አቶ ሙሉቀን ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ተጠናቋል፡፡Post Comments(0)

Leave a reply