...

ጄፍ ቤዞስ ከኃላፊነቱ ሊነሳ ነው

የግዙፉ ቴክኖሎጂ ኩባንያ አማዞን ዋና ስራ አስፈፃሚው ጄፍ ቤዞስ ከኃላፊነቱ እንደሚለቅ ተናገረ፡፡ የዋና ስራ አስፈፃሚነቱን ቦታ አሁን ላይ የአማዞን ዌብ ሰርቪስ ዋና ኃላፊ የሆነው አንዲ ጃሲ የሚይዝ ሲሆን ጄፍ ቤዞስ የኩባንያው ቦርድ ሊቀ መንበር ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የልተጠበቀው ዜና የተሰማው ኩባንያው በተለይ የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ ከፍተኛ ትርፍን እና በዓመቱ የመጨረሻ ሦስት ወራት ብቻም የ100 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ማስመዝገቡን ባሳወቀበት ወቅት ነው፡፡

የ57 ዓመት ጉልምስናው ላይ የሚገኘው ጄፍ ቤዞስ አማዞንን በአውሮፓውያኑ 1994 ከመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በመምራት በምድራችን ካሉ ግዙፍ ኩባንያዎች አንዱ ሊያደርገው በቅቷል፡፡ ያኔ የበይነ-መረብ መፃህፍት መሸጫ ሆኖ ብቅ ያለው ኩባንያው አሁን ላይ በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት፣ ኤሌክትሮኒክስ እና መዝናኛ ላይ ከቀዳሚ ተዋናዮች አንዱና በስሩም ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ቀጥሮ የሚያሰራ ተቋም ነው፡፡ ጄፍ ቤዞስም በዚህ ሰዓት ከሌላኛው የቴክኖሎጂ ሰው ኢለን መስክ ቀጥሎ በ185 ቢሊዮን ዶላር የዓለማችን ቁጥር ሁለት ሀብታም ሰው ሆኗል፡፡ “አማዞን አሁን የሆነውን የሆነው በፈጠራው ምክንያት ነው” የሚለው ጄፍ ቤዞስ ፈጠራዎች በስኬት ከተመሩ ከአንድ ወቅት አስገራሚ ፈጠራነት በተወሰኑ ዓመታት ውስጥ በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚገቡና ለአምጪዎቻቸውም ዘላቂ ጥቅምን የሚያስገኙ እንደሆነ ይናገራል፡፡

ጄፍ ቤዞስ ከቅርብ አመታት ወዲህ ከአማዞን የዕለት ተዕለት ተግባራት እራሱን እያወጣና እንድ ህዋ አሰሳ እና ባለቤት በሆነበት ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ አንዲ ጃሲም የቤዞስ ተተኪ ተደርጎ መታየት ከጀመረ ቆየት ብሏል፡፡ እርሱ የሚመራው አማዞን ዌብ ስርቪስስ ለተለያዩ መንግስታት እና እንደ ኔትፍሌክስ ላሉ ትላልቅ ኩባንያዎችም የኮምፒውቲንግና መረጃ ማከማቸት አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን ከአማዞን አጠቃላይ ሽያጭ የ10 በመቶ ከትርፉም የ52 በመቶውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ምንጭ፡ The GuardianPost Comments(0)

Leave a reply