...

ኢንስቲትዩቱ ያሰናዳው የቅድም ኢንኩዩቤሽን ፕሮግራም ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጀመረ

የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ ኢኖቬተሮችን ለማፍራት ያግዝ ዘንድ ያሰናዳው የቅድመ-ኢንኩቤተር ፕሮግራም የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል፡፡ ለሶስት ቀን በሚቆየው በዚህ የስልጠና መርሃግብር የፈጠራ ሃሳብ ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች፣ ተመራማሪዎች እና የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች የሚሳተፉ ሲሆን፤ የፈጠራ ሃሳባቸውን የሚያሳድጉበት እና ቢዝነስን መምራት የሚችሉበትን ሁለንተናዊ ክህሎት ከስልጠናው ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በመርሃግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የመክፈቺያ ንግግር ያደረጉት የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ቀሬ ኢንስቲትዩቱ በስልጠና፣ በምርምር እና በቢዝነስ መካከል ያሉትን ሁለንተናዊ ክፍተቶች ለሙላት እና የሀገሪቱን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን አንስተው ይህ የቅድም ኢንኩዩቤሽን ፕሮግራምም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ጠቃሚ ሃሳብ ያላቸው የፈጠራ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ወደ ቢዝነስ ማሰደግ እንዲችሉ የሚያግዝ የመማሪያ መድረክ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም እንዳነሱት ኢኖቬተሮች የፈጠራ ሃሳባቸውን መጎልበት እንዲችሉ ሃሳባቸውን ለሌሎች ማጋራት እንደሚገባቸው እና እንደዚህ አይነት መድረኮች ሲገኙም ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡

የስታርት አፕ እና የኢኖቬሽን ፕሮሞሽን ዳይሬክተር የሚያዘጋጀው ይህ ስልጠና ለታሰታፊዎች የፈጠራ አቅምን ለማሳደግ በሚያስችሉ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ስልጠና፣ የቢዝነስ ፕላን አቀራረፅ  እና ሌሎች መሰረታዊ የክህሎት ስልጠናዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ ለሶስት ቀን የሚቆይ ሲሆን ከተለያዩ የመንግስት እና የግል ተቋማት የሚጋበዙ የዘርፉ ባለሙያዎችም ልምድ እና ተሞክሯቸውን ለሰልጣኞች የሚያካፍሉ ይሆናል፡፡ በዛሬው የስልጣና መርሃ ግብርም የቢብሎኪ የቴክኖሎጂ ተቋም ዋና መስራች አቶ ናታን ዳምጠው ስለኢኖቬሽን የመጀመሪያ ሂደቶች እና ስለዘላቂ ቢዝነስ አካሄድ ጠቃሚ ሃሳቦችን  ለሰልጣኖች አካፍለዋል፡፡

ይህ የመጀመሪያ ዙር የቅድም ኢንኩዩቤሽን ፕሮግራም ኢንስቲትዩቱ ቀድሞ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት የፕሮጀክት ሃሳባቸውን አቅርበው ለተመረጡ 25 አመልካቾች የሚሰጥ እና ለተሳትፎዋቸውም ሰርተፍኬት እንዲያገኙ የሚያስችል ስልጠና ሲሆን በቀጣይ ጊዜያትም በተለያዩ መንገዶች መርሃ ግብሩ የሚቀጥል ይሆናል፡፡Post Comments(0)

Leave a reply