...

ከ87 ሺህ በላይ ከፍ ያለው የኮቪድ 19 ምርምር

በአለም ዙሪያ ያሉ ተመራማሪዎች ኮቪድ 19 ከተከሰተ ጀምሮ በወረርሽኙ ዙሪያ ከ87 ሺህ በላይ የሚሆኑ በወረርሽኙ ዙሪያ የተሰሩ ጥናታዊ ጽሁፎችን እንዳሳተሙ ተነገረ፡፡ ይህ መረጃም እስካለፈው የፈረንጆቹ አመት ጥቅምት ወር ድረስ ያለው ነው፡፡ በዚህም ጉዳዩን ሲከታተሉ የነበሩ ተመራማሪዎች በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያክል የምርምር ውጤት በመታተሙ እጅግ እንደተገረሙ ተናግረዋል፡፡

በኦሃዩ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ግሌን ቁጥሩ በጣም አስገራሚ እንደሆነና በሳይንስ ታሪክ ውስጥ ተደርጎ ያማያውቅ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሁሉም በሚባል ደረጃ በአለማችን የሚገኙ የሳይንስ ማህበረሰብ አባላትና ተመራማሪዎች ትኩረታቸውን ወደ ወረርሽኙ ማዞራቸውን ነው፡፡

ተመራማሪዎቹ በጉዳዩ ላይ መረጃ በሰበሰቡበት ወቅት ከተለያዩ ሳይንሳዊ የመረጃ ቋቶች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሰሩ ጥናቶችን ለይተዋል፡፡ በዚህም ከጥር ግማሽ እስከ ሚያዚያ 2020 ድረስ 4875 የጥናት ውጤቶች ወይም አርቲክሎች የታተሙ ሲሆን ይህ ቁጥር እስከ ሀምሌ ግማሽ 2020 ድረስ ወደ 44 ሺህ 13 ከፍ ማለት ችሏል፡፡ በሚያስገርም መልኩ  በአለም አቀፍ ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለው ይህ የምርምር ስራ በ2020ው የጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ 87 ሺህ 515 መድረሱን የተሰበሰበው መረጃ ያመለክታል፡፡

አጥኘዎቹ የኮሮና ወረርሽኝ ጥናትን በ1990ዎቹ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ከነበረው የናኖ ስኬል ሳይንስ ጋር አወዳድረውታል፡፡ በናኖ ስኬል ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች ከ4000 ወደ 90 ሺህ ለማደግ 19 ዓመታት አስፈልጓል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ምርምሮች ግን እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ አምስት ወራት ብቻ ፈጅቶባቸዋል፡፡ በዚህም ቁጥር ላይ የአሜሪካንና የቻይና አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ከአጠቃላዩ ቁጥር ቻይና 43 በመቶውን የሸፈነች ሲሆን የወረርሽኙ ስርጭት በቻይና እየቀነሰ ከመጣ ወዲህ የሚሰሩ ምርምሮችም ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሜሪካም ይህ ጥናት እስከተሰራበት ጊዜ ድረስ የ33 በመቶ ድርሻ ነበራት፡፡

ምንጭ: SciTechDaily  Post Comments(0)

Leave a reply