...

ሆንዳ እጅግ የረቀቀ የተባለለትን ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀስ መኪና ሰርቶ ለገበያ አቀረበ

የጃፓኑ መኪና አምራች ኩባንያ ሆንዳ እስከዛሬ ከተሰሩት ሁሉ በቴክኖሎጂው የላቀ ነው የተባለለትን እራሱን የሚያሽከረክር መኪና ሰርቶ 100 የሚሆኑ ሞዴሎችን ለሽያጭ አቀረበ፡፡ ሌጀንድ የሚል ስያሜ ያለው መኪናው በራሱ መስመሮችን ማለፍ እንዲሁም በአንዳንድ ሁናቴዎችም መስመሮችን ማቋረጥ የሚችል ነው፡፡ በተጨማሪም መኪናው አሽከርካሪው የሚቀርቡለትን የማስጠንቀቂያ መልዕክቶች ተከትሎ መኪናውን ለማሽከርከር ሳይችል ሲቀር በራሱ ፍሬን የሚይዝ ይሆናል፡፡

እንደ ሆንዳ መግለጫ ከሆነ የመኪናውን ስርዓት በሚበለፅግበት ጊዜ 10 ሚሊዮን ያህል የዕውኑን ዓለም አስመስለው በሚያሳዩ ሁናቴዎች ሙከራ የተደረገለት ሲሆን በዕውኑ ዓለምም ለ1.3 ኪ.ሜ ርቀት ያህል በፈጣን መንገዶች ላይ ተሞክሯል፡፡

የተሸከርካሪዎች እራስ ገዝነት ወይም እራስን ችሎ ማሽከርከር ከ0 እስከ 5 ባለው ደረጃ ይለካል፡፡ አንድ መኪና ደረጃ 5 ከተሰጠው ሙሉ በሙሉ እራሱን ችሏል ማለት ነው፡፡ ይህም ሲባል በውስጡ መሪ ወይም ሌላ ምንም አይነት የአሽከርካሪዎች መቆጣጠሪያ የማያስፈልገው ሲሆን ያለ ማንም እርዳታ የበየትኛውም የአየር ፀባይ እና አካባቢ እራሱን ማሽከርከር የሚችል ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ሌጀንድ ደረጃ 3 ላይ ተቀምጧል፡፡

ታድያ የተለያዩ መኪና አምራች ኩባንያዎችም በእራስ ገዝነታቸው ደረጃ 3 የተሰጣቸው ተሸከርካሪዎችን መስራት ችለው የነበረ ቢሆንም ጥቂት ሀገራት ብቻ የእነዚህን ተሸከርካሪዎች ሽያጭ እና አገልግሎት መዋል የሚፈቅድ የህግ ማዕቀፍ ዘርግተዋል፡፡ የሆንዳን ለየት የሚያደርገው ተሸከርካሪው ይፋ የተደረገው በጃፓን ለሽያጭ እንዲቀርብ የሚያስችለውን ፈቃድ ባሳለፍነው ህዳር ላይ ማግኘቱን ተከትሎ መሆኑ ነው፡፡ የሀገሪቱ ተቆጣጣሪሪዎች እራሳቸውን የሚያሽከረክሩ መኪናዎች እርጅና በፍጥነት እየተጫጫነው ለመጣው የጃፓን ህዝብ ደህንነቱ የተጠበቀ መጓጓዣ መፍትሄ ይኖረው ዘንድ በማሰብ ነው ህጉን አሻሽለው መሰል መኪናዎች እንዲንቀሳቀሱ ፈቃድ የሰጡት፡፡

በአሁኑ ሰዓት ከሆንዳ በተጨማሪ የተለያዩ መኪና አምራች ኩባንያዎች እራሱን ማሽከርከር የሚችል መኪና ለመስራት በከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከነዚህ ተቋማት መካከል ቴስላ አንዱ ሲሆን ከተለምዶዎቹ መኪና አምራች ኩባንያዎች ወጣ ባለ መልኩም ግዙፉ የቴክኖሎጂ ተቋም አፕል በጥቂት ዓመታት ውስጥ እራሱን የሚያሽከረክር መኪና ለመስራት ከተለያዩ መኪና አምራቾች ጋር ንግግር እያደረገ ስለመሆኑ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ ማንም አምራች ተሽከርካሪዎቹ ምንም አይነት የአሽከርካሪ እርዳታ አያስፈልጋቸውም በሚባሉበት ደረጃ 4 ላይ የደረሰ ተሽከርካሪን መስራት አልቻለም፡፡

አዳዲሶቹ 100 መኪናዎች የ102 ሺህ ዶላር ዋጋ የተተመነላቸው ሲሆን ለገዢዎች የሚቀርቡትም በሸጦ መልሶ መከራየት (Lease Sale) አኳሀን ይሆናል፡፡ መኪናው እንዲህ በአነስተኛ ቁጥር መቅረቡም ገበያው ላይ ያለ አሽከርካሪ ለሚንቀሳቀሱ መኪናዎች ያለውን ፍላጎት ለመለካት ጠቃሚ ስለመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ምንጭ፤ Tech XplorePost Comments(0)

Leave a reply