...

ታላቁን ግፊት የተቋቋመችው ሰው ሰራሽ ዓሣ

አነስተኛ መጠን ያላት የሲሊኮን ሮቦት እጅግ ጠንካራ ከሆኑት በቀር ማንኛቸውንም ቁሶች ጨፈላልቆ የሚያስቀር ከፍተኛ ግፊት ባለበት የማሪያና ቦይ ወይም ማሪያና ትረንች ውስጥ 10,900 ሜትር ቁልቁል በመስጠም ምንም ሳትሆን ለመውጣት ችላለች፡፡ በቻይው ሾሻንግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በጉሮኢ ሊ የሚመራ የጥናት ቡድን በአንፃራዊ ጫናን የማይችል ለስላሳ አካል ያላቸው ግን ደግሞ በባሕር ውስጥ እጅጉን ጠልቀው ከሚኖሩ የዓሣ ዝርያዎች መካከል በሆነችው የስኔል ዓሣ ላይ በመንተራስ ነው የሮቦቷን ንድፍ የሰራው፡፡ ዓሣዎቹ ከዚህ ቀደም ከባሕር ጠለል በታች እስከ ስምንት ሺህ ሜትር ድረስ ጠልቀው ሲዋኙ ታይተው ነበር፡፡

ባሕር ሰርጓጅ ሮቦቷ ከማንታ ሬይ ዓሣ በሚመሳሰል መልኩ የ22 ሴንቲሜትር ርዝማኔ እና የ28 ሴንቲሜትር የክንፍ ስፋት ያላት ናት፡፡ ሮቦቷ በሲሊኮን ጎማ የተሰራች ሲሆን በውስጧ ያሉት የኤሌክትሮኒክ ግብዓቶቹም እንደሌሎቹ ባሕር ሰርጓጆች በአንድ ሰርኪውት ቦርድ ላይ ከመቀመጥ ይልቅ በአካሏ የተለያየ ክፍል ውስጥ ተሰራጭተው ያሉና በገመዶች የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የጥናት ቡድኑ ባደረገው ሙከራ ከፍተኛ ግፊት ውስጥ በሚኮንበት ጊዜ በጠንካራ ሰርኪውት ቦርድ ላይ ያሉት ትስስሮች የባህር ሰርጓጁ ስስ ብልት ሆነው እንደሚገኙ በማወቃቸው ነው፡፡

ሮቦቷ በውሃ ውስጥ ልክ በስኔል ዓሣ ላይ እንዳሉት ፊኖች ሆነው የሚያገለግሉ ግን ደግሞ የኤሌክትሪክ ከረንት በሚኖር ጊዜ ከሚሰበሰቡ ኤሌክትሪክ አስተላላፊ ፖሊመሮች በተሰሩ ሰው ሰራሽ ጡንቻዎች አማካኝነት የሚንቀሳቀሱ ሁለት ተርገብጋቢ ክንፎቿን በመጠቀም ነው የምትጓዘው፡፡ ይህም ፊኖቹን በ6.3 ዲግሪ የሚያንቀሳቅስና ሮቦቷንም በውሃው ውስጥ እንድትጓዝ የሚያስችል ነው፡፡

እጅግ ጥልቅ የሚባሉትን የባህር ክፍሎች ለመዳሰስ ታስባ የተሰራችው ይህች ሮቦት ለወትሮ ለትልልቆቹ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች ብቻ ይተው በነበረው የዓለማችን ዝቅተኛው የውቅያኖስ ወለል ማሪያና ቱቦ ተሞክራ በስከኬት ማጠናቀቅ ችላለች፡፡ ታድያ ወደ ፊትም ቀልጣፋና ቀላል ክብደት ያላቸው ባህር ሰርጓጅ መርከቦችን ለመገንባት መሰረት እንደምትሆን ተነግሮላታል፡፡

ሮቦቷ በገመድ ሳትታሰር ባደረገቻቸው ሙከራዎች ወቅት 3224 ሜትር ጥልቀት ባለው የደቡብ ቻይና ባህር ክፍል ውስጥ በሴኮንድ እስከ 5 ሴ.ሜ ፍጥነት መዋኘት ችላ ነበር፡፡ የጥናት ቡድኑ በቀጣይም የኮቪድ-19 ክልከላዎች ከተነሱ በኋላ በማሪያና ቱቦ ላይ ተመሳሳይ ሙከራዎችን በሮቦቷ ላይ ለማድረግ አቅዷል፡፡

ምንጭ፤ New ScientistPost Comments(0)

Leave a reply