...

የትኛው እንስሳ ትላልቅ ጆሮዎች አሉት?

የጆሮ ነገር ሲነሳ ብዙዎቻችን የትኛው እንስሳ ነው በዓለማችን ትላልቅ ጆሮችን የያዘው ብንባል ዝሆን ብለን መመለሳችን አይቀርም፡፡ አልተሳሳትንም፤ የአፍሪካ ዝሆኖች ምድራችን ላይ ካሉት እንስሳት ሁሉ የላቀ ጆሮን ተሸክመዋል፡፡ ሆኖም ጥያቄው ተሻሽሎ ከሰውነት መጠን አንፃር የትኛው እንስሳ ትላልቅ ጆሮዎች አሉት ተብሎ ከተጠየቀ ግን መልሱን ዝሆን ሳይሆን መኖርያውን በቻይና እና ሞንጎሎያ ያደረገው ባለ ረጅም ጆሮ ጀርቦአ (Euchoreutes Naso) የተሰኘው ነፍሳትን አድኖ ተመጋቢ የአይጥ ዝርያ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ባለ ረጃጅም ጆሮ ጀርቦአ ጭራው ሳይቆጠር ከራስ ቅል እስከ ቂጡ ያለው ርዝመቱ ወደ 10 ሴ.ሜ ብቻ ይጠጋል፡፡ በዚህ አነስተኛ አካሉ ላይ ያሉት ጆሮዎቹ ታድያ ከ3.8 እስከ 5 ሴ.ሜ ይሆናሉ፡፡ እነዚህን ጆሮዎች ከመላው የሰውነት አካሉ ጋር ስናነፃፅራቸው ከ40 እስከ 50 በመቶውን ይይዛሉ እንደማለት ነው፡፡ በዚህም ነው ከማንኛውም እንስሳ በላቀ ከፍተኛ የጆሮ ግዝፈት ምጣኔ አለው ያሰኘው፡፡ ለንፅፅር የአፍሪካ ዝሆኖችን ብንመለከት የጆሮዋቸው ርዝመት 1.2 ሜትር ቢሆንም በአማካኝ ከ6 እስከ 7.5 ሜትር ከሚደርሰው የሰውነት ርዝመታቸው ጋር ስናወዳድረው ከአጠቃላይ ሰውነታቸው ጋር ያለው የርዝመት ምጣኔ 17 በመቶ ሆኖ እናገኘዋል፡፡

እንዲህ ያሉ ትላልቅ ጆሮዎች ጀርቦአም ሆነ ሌሎች በሞቃትና ደረቅ አየር ንብረት ባለባቸው ስፍራዎች ውስጥ የሚኖሩ አጥቢ እንስሳት ሙቀቱን መከላከያ መሳርያዎቻቸው ናቸው፡፡ እንደ አፍሪካ ዝሆን፣ ፌኔክ ቀበሮ፣ ባለ ረጅም ጆሮ ጀርቦአ ያሉት እንስሳት የደም ስሮች በታጨቁባቸው ጆሮዎቻቸው አማካኝነት ከመጠን ያለፈ የሰውነት ሙቀትን ያስወግዳሉ፡፡ ይህም ሲባል የእንስሳቱ ጆሮዎች ግዙፍ፣ ቀጫጭን እንዲሁም በውስጣቸው ትናንሽ የደም ቧንቧዎችን የያዙ ናቸው፡፡ ታድያ ደም በእነዚህ የጆሮ ውስጥ ባሉት የደም ስሮች በሚዘዋወርበት ሰዓት ሙቀትን ወደ አየር ስለሚለቅ የእንስሳውን ሰውነት ያቀዘቅዘዋል፡፡ እንስሳው እየሞቀ በመጣ ቁጥርም እነዚህ የጆሮ ውስጥ ደም ቧንቧዎች ይበልጡን እየሰፉና ወደ ውጭ የሚለቁት የሙቀት መጠንም እያደገ ይመጣል፡፡ በተቃራኒ አየሩ ቀዝቃዛ በሚሆንባቸው የምሽት ሰዓታት ወይም ሌሎች ቀዝቀቃዛማ ወቅቶች ግን የጆሮ ውስጥ ደም ስሮቻቸው በመኮማተር የሰውነት ሙቀታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ያስችሏቸዋል፡፡

ነገሩን ስንመለከተው ሙቀትን በጆሮ መከላከሉ ለእነዚህ የበረሀ ውስጥ እንስሳት እጅግ አዋጭ ስልት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንበልና እንስሳቱ ልክ እንደ ሰው ልጆች ሙቀትን በላብ አማካኝነት የሚያስወጡ ቢሆን ኖሮ ኑሮዋቸው በረሃና ውሃ እንደልብ በማይገኝባቸው ስፍራዎች እንደመሆኑ ለውሃ እጦት ይዳርጋቸው ነበር፡፡ ትላልቅ ጆሮዎችን መጠቀሙ ግን የሰውነታቸውን ውሃ እንዳያባክኑ ያደርጋቸዋል፡፡

ሙቀትን ከመከላከል በተጨማሪ የጀርቦአዎች ጆሮ መርዘም አድነው ከሚመገቧቸው አልያም እነርሱን ሊያድኗቸው ከሚችሉ እንስሳት የሚመጡ ባለ ዝቅተኛ ፍሪኩዌንሲ ድምፆችን ለመስማትም ያስችላቸዋል፡፡

ምንጭ፤ Live SciencePost Comments(0)

Leave a reply